“ጤፍን ሰዳ የምታሳድደው ኢትዮጵያ

የጤፍ ምርቱን ማሳ ላይ እየለየ ያለ ገበሬImage copyrightGETTY IMAGES

መንግሥት ውልደቱም እድገቱም ኢትዮጵያ በሆነው ጤፍ ላይ በአምስት የአውሮፓ ሃገራት የባለቤትነት መብት ያስመዘገበው የኔዘርላንድ ኩባንያ ላይ በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ክስ ሊመሰርት እንደሆነ አስታውቋል።

መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከኩባንያው ጋር ያለውን ጉዳይ ለመፍታት ያደረጋቸው ጥረቶች ሊሳኩ ባለመቻላቸው መሆኑንም ገልጿል።

ውሳኔውን ተከትሎ መንግሥት ክስ በመመስረት የሚጠብቀው ውጤት ምንድን ነው? ከሃገሪቱ የገንዘብና የቴክኒክ አቅም ማለትም ከዓለም አቀፍ ግልግል ዳኝነት ልምድ አንፃር ኢትዮጵያ ይሳካላታል ወይ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።

ጤፍ እንዴት ከኢትዮጵያ እጅ ወጣ?

እንደ አውሮፓውያኑ 2004 ላይ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲቲዩትና የግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል(HPFI) ከተባለ የኔዘርላንድ ኩባንያ ጋር ስምምነት ያደርጋሉ።

ስምምነቱ የኔዘርላንዱ ኩባንያ የተለያዩ የጤፍ ዝርያዎችን በመጠቀም ከጤፍ ኬክ ኩኪስና ሌሎችም መሰል ምግቦችን በማምረት ለገበያ እንዲያቀርብና ትርፉን ለኢትዮጵያ እንዲያጋራ እንዲሁም በየጊዜው ለኢትዮጵያ የባለቤትነት መብት ክፍያ እንዲከፍል ነበር።

በጤፍ የባለቤትነት መብት ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የጤፍ ዝርያዎች እንዲሁም ከጤፍ አመራረት ጋር የተያያዙ ባህላዊ እውቀቶች ባለቤትነት የኢትዮጵያ ጤፍ አምራቾች ሆኖ እንደሚቀጥል ስምምነቱ ያስቀምጣል።

በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ከተወሰዱት የጤፍ ዘሮች የሚፈጠሩ አዳዲስ ዝርያዎች ባለቤትነት ደግሞ የኢትዮጵያና የኔዘርላንዱ ኩባንያ እንደሚሆን በስምምነቱ ተመልክቷል።

ነገር ግን ከዚህ በኋላ ኩባንያው ስምምነቱን በሚፃረር መልኩ መንቀሳቀስ ጀመረ፤ በመቀጠልም ሙሉ በሙሉ ከሚመለከተው የኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋም ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ። በማስከተልም መጀመሪያ በኔዘርላንድ ከዚያም በጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ኦስትሪያና ጀርመን የጤፍ ምርት ባለቤትነት መብት ወሰደ።

በመጨረሻ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ያደረገው ኩባንያ (HPFI) መክሰሩን አሳውቆ ሲዘጋ በጤፍ ውጤቶች ላያ ያገኘውን የባለቤትነት መብት Vennootschap Onder Firma(VOF)ለተባለ ሌላ ድርጅት አስተላለፈ።

በዚህ መልኩ ከኢትዮጵያ እጅ የወጣውን የጤፍ ዱቄት አዘገጃጀት የባለቤትነት መብት ለማስመለስ ለረዥም ጊዜያት የተደረገው ድርድርና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን ከጥቂት ቀናት በፊት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አቶ ጌታሁን መኩሪያ ለተወካዮች ምክር ቤት ገልፀዋል።

ስለዚህም መብቱን ለማስመለስ ብቸኛው አማራጭ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የፍትህ ተቋም መውሰድና የኔዘርላንዱን ኩባንያ መክሰስ እንደሆነ፤ ይህን ለማድረግም እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ማንን? የት ነው የምትከሰው?

በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ግልግል ዳኝነት አማካሪ የሆነችው ወ/ት ልዩ ታምሩ መንግሥት ይህን ጉዳይ በዓለም አቀፍ ግልግል ዳኝነት እወጣዋለሁ ካለ ሁለት ነገሮችን ማጤን ያስፈልጋል ትላለች።

የመጀመሪያው ጥያቄ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ያደረገው ኩባንያ አሁን ሥራ ላይ ካለመሆኑ ጋር የሚገናኝ ነው።

“ስለ ክሱ ዜና ላይ እንደተመለከተው መንግሥት ክሱን የሚመሰርተው መቀመጫውን ፓሪስ ባደረገው በዓለም አቀፉ የግልግል ዳኝነት ማዕከል ነው። እዚህ ቦታ ላይ ሄዶ የሚከስ ከሆነ ደግሞ መክሰስ የሚችለው በውሉ ላይ ስምምነት ያደረገውን ኩባንያ ነው። ያ ኩባንያ ደግሞ በኪሳራ ተዘግቷል። እዚህ ጋር አንድ ትልቅ ችግር ይነሳል” ትላለች ልዩ።

የተዘጋና የሌለን ኩባንያ እከሳለሁ ማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ትገልፃለች።

በሁለተኛነት የምታነሳው ደግሞ መንግሥት ጉዳዩን በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት እጨርሰዋለው ሲል የግልግል ዳኝነት ተቋሙ ተግባርና ስልጣንን ታሳቢ አድርጎ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ነው።

ልዩ እንደምትለው ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት መብት ያለው፤ ጉዳትን የመመልከትና የማስላት ነው። የባለቤትነት መብትን የመንጠቅ ስልጣን የለውም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ማድረግ ያለበት የጤፍ ባለቤትነት መብትን ማስመለስ ከሆነ ነገሩ የባለቤትነት መብቱን የሰጠው ማነው? ወደ ሚለው ያመራል።

ለኔዘርላንዱ ኩባንያ የጤፍ ባለቤትነት መብቱን የሰጠው ደግሞ የአውሮፓ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ (EPO) ነው።

የሚያዋጣው ይህ ተቋም በምን አግባብ ለኩባንያው መብቱን ሰጠው የሚለው ላይ አትኩሮ በዚህ አቅጣጫ መሄድ እንደሆነ ታስረዳለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ ከመጀመሩ በፊት እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ሊያስብበት ይገባል ትላለች።

ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ተሞክሮና አሁን በአገሪቱ ካለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት አንፃርም ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቀው ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነትን መምረጥ በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባም ታስረዳለች።

“ምንም እንኳ ኢትዮጵያዊያን ያሉበትን የጥብቅና ድርጅት መንግሥት ተጠቅሞ ቢያውቅም አብዛኛውን ጊዜ የውጭ ሃገር ሰዎችን ነው የሚጠቀመው” የምትለው ልዩ አሁን ግን መንግሥት ስለ ጤፍ ምንነት የሚያውቅ፣ ስለ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃና መብት የግልግል ዳኝነትም እውቀት ያለው ኢትዮጵያዊ የህግ ባለሙያን በጉዳዩ ሊያሳትፍ ግድ ነው የሚል አቋም አላት።

እንጀራImage copyrightGETTY IMAGES

የኢትዮጵያ የማሸነፍ እድል ምን ያህል ነው?

መንግሥት ክስ ሊመሰርት ስላቀደበት ስትራቴጂ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም፤ በዚህ ነገር ውስጥ ኢትዮጵያ ሦስት ጉዳዩች አሏት ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ብሩክ ኃይሌ።

የመጀመሪያው ባደረጉት ስምምነት መሰረት በኔዘርላንዱ ኩባንያ ሊከፈላት ይገባ የነበረው ገንዘብ ለኢትዮጵያ አለመከፈሉ። ሁለተኛው በጤፍ አዘገጃጀት ላይ የተገኘው የባለቤትነት መብት ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ኩባንያው ያገኘው አዲስ የጤፍ ዝርያ ላይ የወሰደው የባለቤትነት መብት ናቸው።

ኢትዮጵያ በውሉ መሰረት ከኔዘርላንዱ ኩባንያ ማግኘት የነበረባት ገንዘብ እንዲሁም የምርምር ድጋፍ ጉዳይን ሲያስቡት ነገሩ ሰዶ ማሳደድ እንደሚሆን ዶ/ር ብሩክ ይናገራሉ።

“ጤፋችንን ስንልክ ቀድመን ክፍያውን መቀበል እንችል ነበር። ይህ ለምን እንዳልተደረገ አላውቅም። ውሉን ስንገባ ማግኘት ያለብንን የገንዘብ ጥቅም ቀድመን እንድናገኝ መደረግ፤ ኩባንያው የሚያሲዘው ዋስትናም መኖር ነበረበት” ይላሉ።

የሚገባንን ክፍያ አላገኘንም ከተባለ እሳቸውም ከኢትዮጵያ ጋር ውል የገባው ኩባንያ በኪሳራ የተዘጋ መሆኑም የክስ ሂደቱን እንደሚያከብደው ይሰማቸዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ኩባንያው በኪሳራ የተዘጋበትና የባለቤትነት መብቱን ለሁለተኛው ኩባንያ ያስተላለፈበት መንገድ የኔዘርላንድን የኪሳራ ህግ ያልተከተለ ነው የሚል ነገር ላይ ካልተደረሰ በቀር በዚህ ረገድ ያለው ተስፋ የመነመነ ነው።

የሚያስኬድ የሚመስላቸው ነገር በጤፍ አዘገጃጀት (እንደ ጤፍ ኬክና ኩኪስ ዝግጅት) ላይ ኩባንያው ያገኘው የባለቤትነት መብትን ማስመለስ ነው። ምክንያቱም ይህ እውቀት በሰፊው የኢትዮጵያ ጤፍ አምራች ዘንድ የሚታወቅ ነውና።

በተጨማሪም በጣልያን፣ በእንግሊዝም ሆነ በኔዘርላንድ ህግ የባለቤትነት መብት ለመስጠት አንድ ነገር አዲስ ፈጠራ አዲስ እውቀት መሆን ስለሚገባው ከዚህ የህግ አግባብ ተነስቶ ነገሩን አጠንክሮ መያዝ ይቻላል ብለው ያምናሉ ዶ/ር ብሩክ።

“የጤፍ አዘገጃጀት ነባር የአገር ውስጥ እውቀት መሆኑን በማስረጃ በማስረገጥ ኩባንያው የጤፍ ዱቄት አዘገጃጀት ላይ ያገኘውን የባለቤትነት መብት ውድቅ ማስደረግ የሚቻል ይመስለኛል”ሲሉ ያክላሉ።

ይህን የባለቤትነት መብት ውድቅ ብታስደርግ ኢትዮጵያ ምን ታገኛለች?

ዶ/ር ብሩክ እንደሚሉት የባለቤትነት መብቱን ከኔዘርላንዱ ኩባንያ ብታስነጥቅም ኢትዮጵያ በቀጥታ የምታገኘው የገንዘብ ጥቅም አይኖርም። ምክንያቱም ነባርና የቆየ እውቀት ነው ከተባለ ኢትዮጵያም ዳግም አዲስ ነው ብላ ልታስመዘግብና የባለቤትነት መብት ልትወስድበት አትችልም።

“ከኢትዮጵያ የወሰዱትን ዘር በመጠቀም ምርምር አካሂደው ያገኙት አዲስ ጤፍ የባለቤትነት መብትን በማስነጠቅ በኩልም የሚሳካልን አይመስለኝም። ምክንያቱም በአውሮፓ ህግ መሰረት በዚህ አይነት ምርምሮች የሚገኙ አዳዲስ ዘሮች ጥበቃ አያገኙም የሚል ነገር የለምና” ይላሉ።

በዚህ ረገድ በብዝሃ ህይወት ዙሪያ የዓለም አቀፍ ህግ ደካማ መሆንና ሃገራት ዓለም አቀፍ ግዴታ የሌለባቸው መሆኑ ኢትዮጵያን ተጋላጭ እንዳደረጋት ያስረዳሉ።

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የግልግል ዳኝነት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዮሃንስ ወልደ ገብርኤልም የጤፍን የባለቤትነት መብት በማስመለስ ኢትዮጵያ ተስፋ የላትም ሲሉ ይደመድማሉ።

ምክንያታቸው ግን ከሌሎቹ አስተያየት ሰጪዎች ለየት ያለ ነው።

“እንኳን እንዲህ ያለ የተወሳሰበና ትልቅ አቅም የሚጠይቅ ክስ ቀርቶ፤ ተራ ጉዳዮችን እንኳ በሚገባ መመልከት የማይችል አቃቤ ህግ ባለበት ይህ ክስ ዘበት ነው” በማለት የኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኩባንያን እከሳሁ ማለቷን የሚገልፀውን ዜና እንደ ቀልድ እንደተመለከቱት ይናገራሉ።

በጤፍ ይብቃ

ረዘም ላሉ ዓመታት በስዊዘርላን በርን ዩኒቨርሲቲ በጤፍ ላይ ምርምር እያደረጉ የሚገኙት ዶ/ር ዘሪሁን ታደለ ከሁለት ዓመታት በፊት የኔዘርላንዱን ኩባንያ በመቃወም ከአሜሪካ ጀምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ ፊርማ ሲያሰባስቡ እንደነበርና በዚህ እሳቸውም መሳተፋቸውን ያስታውሳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ብዙ ጊዜ እንደዚህ ያለ የባለቤትነት መብት ማጣት ችግር ውስጥ የሚገባው ከትምህርት ተቋማት ሳይሆን ከግል ኩባንያዎችና መንግሥታዊ ካልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ሲገባ ነው ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የእህል ዘሮችን ለመጠበቅ የሚያስችል ሥራ ለመስራት ጅምሮች መኖራቸውን “እርሻ ምርምር ከሚገኙ የሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ልክ ዲኤንኤ ሰዎችን እንደሚገልፅ ሁሉ የእህል ዘሮችን በዚሁ መንገድ ወደ ኋላ ሄዶ መለየት የሚያስችል ይሆናል ስራው” በማለት እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች አመልክተዋል”