//// ጉግሣ ይማም ////

ይርጋ አበበን ማን ገደለው ?
ለምንስ ተገደለ ?
ታምራት ላይኔ ይጠየቅ እርቆ ሳይሄድ ወደ ጒድጓድም ሳይወርድ

” የኢህዴኑ ይርጋ አበበ ታዬ /ሀው ጃኖ/ እና ለመስዋዕትነት ያበቃው የህወሃት የበላይነት ተቃዉሞው
(ከዘሀበሻ ድረ ገጽ በኃይሉ ከበደ)

ይርጋ አበበ ታዬ በበረሃ ስሙ ሀው ጃኖ በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር የራያና ቆቦ አውራጃ መናገሻ በነበረችው በአላማጣ ከተማ ተወለደ። የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን /ኢህዴን/ ወይም በአሁኑ አጠራር ብአዴንን በ1975 ዓመተ ምህረት መጨረሻ ላይ ተቀላቀለ። ይርጋ ሕይወቱ እስካለፈበት እስከ 1983 ዓመተ ምህረት ድረስ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሰራ ቢሆንም አብዛኛው ጊዜውን ያሳለፈው ሰራዊቱን በመምራት ነበር።በነበረው የወታደራዊ አመራር ብቃትና የትምህርት ዝግጅት ወሳኝ ከሚባሉት የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴዎች መካከል አንዱ የነበረና ኢህአዴግ ወደ መሃል አገር መገስገስ በጀመረበት ጊዜ በአገሪቱ ይካሄድ የነበረው ጦርነት ከህወሃትና ከኢህዴን በተውጣጡ የማዕከላዊ ኮሚቴዎች ወይም የደጀን አመራር ይመራ ስለነበር ይርጋም የዚህ የግንባር አመራር አባል ነበር።

ይርጋ በተለያዩ ዓውደ ውጊያዎች ሰራዊቱን በመምራት በብዙ ዓውደ ውጊያዎች የተሳተፈ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ተራ ተዋጊ ታጋይ በነፍስ ወከፍ መሳሪያ ምሽግ ድረስ እየገባ ሀው ጃኖ እያለ በመፈከር በብቃት ያዋጋና ይዋጋ ስለነበር በኢህዴን ሰራዊት ውስጥ ይበልጥ የሚታወቀው ሀው ጃኖ በሚለው ቅጽል ስም ሲሆን ትርጉሙም በራይኛ የጃኖ ወንድም ማለት ነው። ጃኖ በጣም የሚወዳት ታላቅ እህቱ ነች። ከፍተኛ የጦር አዛዥ ሆኖ እያለ እንደ ተራ ተዋጊ በሚያደርገው የውጊያ ተሳትፎ ብዙ ጊዜ በኢህዴን ታጋዮች “ጀብደኛ ነህ ” እየተባለ ይገመገም ነበር። ይርጋ ኢህዴን ነበሩኝ ከሚላቸው ወታደራዊ ስትራቴጅስቶች አንዱ እንደነበር ይታወቃል።ዓበይት የሚባሉ ዓውደ ውጊያዎች እንዲመራም ይደረግ ነበር :: ለአብነት ያህል “ሰላም በትግል” ኦፕሬሽን በመባል የሚታወቀውና ኢህአዴግ በ1981 ዓመተ ምህረት ክረምት ላይ ከማይጨው እስከ ወልዲያ ያካሄደው ኦፕሬሽን በዋነኛነት የተመራው በህወሃቱ ኃየሎም አርአያና በኢህዴኑ ይርጋ አበበ /ሀው ጃኖ/ ነበር።

ይርጋ ህወሃት በኢህዴን ውስጥ ያደርገው የነበረው የበላይነት በተለይም የነ በረከት ስምዖን፣ታደሰ ጥንቅሹ፣ህላዌ ዮሴፍ የመሳሰሉት የመለስ ዜናዊ ተላላኪዎችን አካሄድ አምርሮ ከሚቃወሙ የኢህዴን አመራሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነበር። ኢህዴን ሌላውን ህዝብ ነጻ ለማውጣት ቅድሚያ ራሱን ነጻ ሊያውጣ ይገባል ብሎም የሚሞግት ነበር። በተለይም በኢህአዴግ ውስጥ የህወሀት የበላይነት በግልጽ እየተንጸባረቀ ነው፣ የኢህዴን አመራርም ይህን ሁኔታ እስከመቼ በዝምታ እያየ ያልፈዋል? የሚል ጠንከር ያለ አቋም በመያዝ በጽሁፍ ጭምር ከመለስ ዜናዊና ከታምራት ላይኔ ጋር በድፍረት ተሟግቷል:: ማንም ሊገምተው እንደሚችል ይህ ዓይነት አቋም ለዚያውም ወደ ትግራይ ሊያካልሉት ከሚቋምጡለት በለምለምነቱና በሜዳማነቱ ለግብርናም ሆነ ለከብት እርባታ አመች ከሆነው የተፈጥሮ ሐብት ባለቤት ከሆነው ከራያ ማህበረሰብ የወጣው ይርጋ አበበ ይህ ዓይነት አቋም መያዙ ህወሃትን እንቅልፍ የሚያስተኛ አልነበረም። ኋላ ላይ እንደምገልጸው ይርጋ በ1983 ዓመተ ምህረት በህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ትዕዛዝ እስከ ተገደለበት ድረስ አሁን ወደ ትግራይ የተካለሉት ዋጃ፣አላማጣና ኮረም በኢህዴን ክፍለ ህዝቦች ነበር የሚተዳደሩት። ለምሳሌ ያህል ይርጋ ማዕከሉን ወልዲያ አድርጎ የደጀን አመራር በነበረበት ጊዜ ኋላ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበረው ዮሴፍ ረታ /ገይድ/ በ1982 ዓመተ ምህረት የአላማጣ ወረዳ ከፍለ ህዝብ ወይም አስተዳዳሪ ነበር።

በአንድ ወቅት የኢህዴን ክፍለ ህዝብ የነበረና በ1990 ዓመተ ምህረት በተከሰተው የኢትዮ_ኤርትራ ጦርነት ኤርትራዊ ነህ ተብሎ ከኢትዮጵያ የተባረረው ጋዜጠኛ ሰናይ ገብረ መድህንም አላማጣ በኢህዴን አስተዳደር እንደነበረችና እሱም የአላማጣ ወረዳ ክፍለ ህዝብ እንደነበር ከSBS አውስትራልያ ራዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልጿል። ሌሎችም መጥቀስ ይቻላል። እዚህ ላይ የምንገነዘበው ይርጋ በሕይወት በነበረበት ወቅት ህወሃቶች ይህንን አካባቢ ወደ ትግራይ ለማካለል አልደፈሩም ነበር። ለምን እንደዚህ እንደሆነና ለምንስ ሁኔታው ተለወጠ? እንደ ማዕከላዊ ኮሚቴነቱና የአካባቢው ተወላጅነቱ እንዲሁም በኢህአዴግ የህወሃትን የበላይነትና ህወሃት በኢህዴን ላይ ያደርገው የነበረው ጣልቃ ገብነት ከመቃወሙ አንጻር የይርጋ አቋም ምን ይመስል ነበር? ፍጻሜውስ እንዴት እንደዚህ ሊሆን ቻለ የሚሉትን ጉዳዮች በዝርዝር ሊያስረዱን የሚችሉት አቶ ታምራት ላይኔ ብቻ ናቸው _ በወቅቱ የድርጅቱ መሪ ስለነበሩና አሁን ባሉበት ሁኔታ እውነቱን የመናገር ነጻነት ስላላቸው። አንድ ቀንም ያደርጉታል የሚል ተስፋ አለኝ።

ከላይ ይርጋ ኢህዴንን በመወከል የሰላም በትግል ኦፕሬሽን ከኃየሎም አርአያ ጋር በጋራ እንደመሩት ጠቅሻለሁኝ:: በጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ ይመራ የነበረው የ605ኛ ኮር ጳጉሜን 3፣1981 ዓመተ ምህረት አላማጣ ላይ ተደምስሶ ወደ ቆቦ ሲያፈገፍግ ኃየሎም አርአያ የራሺያ ስሪት በሆነች ክፍት ዋዝ መኪና ይርጋ አበበ ደግሞ ሽሮ ቀለም ባላት ፒክ አፕ ሆኖ አላማጣ ሼል ማደያ ለተወሰነ ሰዓት ዕረፍት አድርገው ስለነበር ይርጋን የራያ ሰዎች በደስታና ፈገግታ እየተቀባበሉ ሲስሙት በዓይኔ አይቻለሁኝ። ተስፋ ያደረጉበትም ይመስላል _ ህወሃትን በተመለከተ ራያዎች በሩቁ/በወሬ ይሰሙት የነበረው ራያዊ ማንነታቸውንና ባህላቸውን እንደሚያጠፋ /እንደሚጨፈለቅና ራያነት የሚለውን ወደ ትግራዋይነት እንደሚቀይረው ስጋቱ የነበራቸው ይመስላል። ይርጋን የመሳሰሉ ሰዎች በኢህዴን ውስጥ መኖር ደግሞ ራያዎች ይህ ሊሆን እንደማይችል ተስፋ ነበራቸው _ አልሆነም እንጂ!የሆነው ሆኖ ህወሃትና ኢህዴን የሰላም በትግል ኦፕሬሽን በጋራ ሲያካሂዱ በውጊያው አመራር ሂደት ላይ በኃየሎምና በይርጋ መካከል የተወሰኑ ያለመግባባቶች ተከስተው ነበር _ የተለመደው እኛ የበላይ ነን ዓይነት አካሄድና ይርጋ ደግሞ እሱን ተወው! በሚል። ይህም ነገር አቶ ታምራት ድረስ ደርሶ ጦርነቱ እስኪጠናቀቅ ተስማምተው እንዲሰሩ መመሪያ ቢሰጥም መስማማት ባለመቻሉ ይርጋም በዚህ መልኩ ከህወሃቶች ጋር አልሰራም በማለቱ ነገሮች ይበልጥ እየከረሩ መሄድ ጀመሩ።

ከዚህ በኋላ ነበር ይርጋ ወልዲያ ላይ ሆኖ የግንባሩ የትጥቅና ስንቅ ሃላፊ እንዲሆን የተደረገው። ሆኖም ከህወሃት ጋር የነበረው አለመግባባት ይበልጥ እንዲያገረሽ ያደረጉ ሁለት ነገሮች ወልዲያ ላይ ተከሰቱ። የመጀመሪያው ክስተት የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደጀን አመራር የነበረው ይርጋ አበበ ሳያውቀው በወቅቱ ክፍለ ኢኮኖሚ ተብሎ ይጠራ በነበረው ክፍል ተመድባ ትሰራ የነበረች እሌኒ የተባለች ተራ የህወሃት ታጋይ በምርኮ የተገኙ የተለያዩ ንብረቶችን አስጭና ወደ ትግራይ ልትልክ ስትል በአካባቢው ያልነበረው ይርጋ ባጋጣሚ ቦታው ላይ ይደርስና የሆነውን ይመለከታል። ምንድን ነው እየተጫነ ያለው? ወዴት ነውስ የሚጫነው? ማንስ ፈቅዶ ነው? ሲል ይጠይቃል። እሌኒም ወደ ትግራይ እንዲጫን አለቆቼ አዘዋል የሚል መልስ ስትሰጥ፡ይርጋም የተጫነው እንዲራገፍ በማዘዝ ያለሱ ፈቃድ አንድም ንብረት እንዳይንቀሳቀስ በማዘዙ እሌኒም የሆነውን ነገር ለመለስ ዜናዊ በሬዲዮ ሪፖርት በማድረጓ መለስም ይርጋ እያደረገው ያለው ነገር የማያዛልቅ እንደሆነ ኢህዴን ይርጋ ላይ የማያወላዳ ዕርምጃ እንዲወስድ ማስጠንቀቁ ይነገራል።”

Image may contain: 1 person, suit, eyeglasses and closeup
LikeShow more reactions