ትዝብት ዓይን ያወጣ ውሸት ለሚሊዮን ስደትና ሞትም ኢሳትን ተጠያቂ ለማድረግ እየታሰበ መሰለይ ?

Gizachew Abebe Ethiopia

የሚሊዮን ሹርቤ ጉዳይ!

የሚሊዮን ሹርቤ ጉዳይ ወደ ውዝግብ አምርቷል። ኢሳቶች ከዚህ ውዝግብ ብዙ ይማራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የኢሳት ሰዎች የተሰደዱ ጋዜጠኞችን ስለ መርዳት ሲያወሩ እየሰማን ብንቆይም ጠብ ያለ ነገር ሳይኖር ጊዜያት አልፈዋል። ከወሬ ያለፈ ምንም ነገር እንዳልተደረገ የሚያጋልጠው ትልቅ ነገር የሚሊዮን ሹርቤን መሞት ተከትሎ የመጣው ጉዳይ ነው። የሚሊዮን መሞት ሲሰማና ጓደኞቹ አስከሬን መላኪያ አጣን ብለው ችግራቸውን ሲያሰሙ ኢሳት ላይ ሲወራ የነበረው ነገር እንደገና አንሰራራና ‘ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ’ እንደ አዲስ ሩጫ ታየበት። እዚህ ላይ የኢሳት ቋሚ ችግርም አብሮ መታየት ጀመረ።
ኢሳት ማንም ሊክደው የማይችል ነገር ቢኖር ችግሮች ያሉበት መሆኑና በውስጡ መመካከር የሚባል ነገር አለመኖሩ ነው። አንድ ግለሰብ ስሜቱ በነዳው (በመራው) አቅጣጫ ይሄዳል ያወራል፣ ሌሎች አያርሙትም አይተቹትም እነሱም በራሳቸው ስሜት ይነዳሉ።
ከኢሳት ችግሮች አንዱ አንዳንድ ግለሰቦች ሚዲያውን ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ አድርገውት መታየታቸው ነው። አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ፣ ራሳቸውን ታላቅ አስመስሎ ለማቅረብ፣ ራሳቸውን የሰብዓዊነት ዓምድ አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ይታያል። እነዚህ ሰዎች ይህን ባህሪያቸውን ይዘው ወደ ኢሳት ከተፍ የሚሉት ‘ትኩረት የሚስብ’ ነገር ሲመጣ ነው። በኢትዮጵያውያን ላይ ችግር ሲደርስ እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች ድራማቸውን ይዘው ወደ ኢሳት ይመጣሉ። ከዚያም ቢያንስ ለሳምንትና ለሁለት ሳምንት እዚያው ይከርማሉ። ይህ የመንቀዥቀዥ ፖለቲካ ብቻ እንጅ ምንም ቁም ነገር የለውም። የመንቀዥቀዥ ፖለቲካ ከሚሊዮን አስከሬን ጋር በተያያዘ ችግር ፈጥሮ ታይቷል። የመንቀዥቀዥ ፖለቲካ ይሉኝታ የለውም። ካልተወገደ እንዲህ በሰዎች ችግር ሲነግድ ይከርማል። መንቀዥቀዥ ማመዛዘንን ይነሳል። የመንቀዥቀዥ ፖለቲካ የጭቃ ውስጥ እሾኽ-የውሃ ስር ድንጋይ ነውና ሳይታይና ሳይታሰብ ብዙ አደጋ ያደርሳል። ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚሊዮንን ቤተሰቦች ለመርዳት ብለው ይሁን ለማጽናናት በማሰብ ያዋጡት ገንዘብ ሜዳ ላይ የቀረው ገዥው ቡድን የሌላውን ወገን ፕሮፓጋንዳን ለመከላከል ሲል ጣልቃ በመግባቱ ብቻ ሳይሆን የጊዜውን ሁኔታና በዚህ ቤተሰብ ላይ ያጋጠመውን ችግር ችላ ያለ የመንቀዥቀዥና ራስን የማስተዋወቅ ዘመቻ በመካሄዱም ጭምር መሆኑ መካድ የለበትም። የብዙ በውጭ ያሉ ሰዎች ደግነት በጭቃ ውስጥ እሾኾች ተሰናክሏል። በመሰናከልም አልተገታም። የሚሊዮንን ቤተሰቦችና ወዳጆች አደጋ ውስጥ በመክተትና እነሱን በማጥላላት መካከል ዥዋ ዥዌ ጨዋታም እየታየ ነው።
ለሁሉም የሚሊዮንን ቤተሰቦች ተወት ማድረግ ተገቢ ነው። እናንተ አሜሪካ ውስጥ አንድ ነጭ “ችምፕ” ወይም “ኤፕ” ሲላችሁ ዝም ብላችሁ ወይም ያልሰማችሁ መስላችሁ ለመጓዝ እንደምትወስኑት ሁሉ የሚሊዮን ቤተሰቦችም ሆኑ ሌላው ኢትዮጵያዊ ዝም የሚልበት ነገር ሊኖር እንደሚችል ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው። በአሜሪካ ጎዳናዎች ላይ ጥቁሩ ‘ጦጣ’ ‘ችንፓንዚ’ የብሎ በጥይት በተደጋጋሚ ድፍት ብሎ ሲቀር ‘እዚህና እዚያ’ ከመሆን ብላችሁ በማመዛዘን ቻል አድርጋችሁ በጥንቃቄ እንደምትኖሩትን ለጥቃቄ ስትሉ አደጋውን ብቻ ሳይሆን አደጋውን ተከትሎ የሚመጣውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለዜና እንኳ እንደማታቀርቡ ሁሉ፣ ከዚህም አልፋችሁ አሜሪካ የሕግና የሰላም አገር ብላችሁ እንደምትሰብኩት ሁሉ የሚሊዮን ወዳጅና ዘመዶች ‘ለመኖር ሲሉ’ ይሁን ‘አምነውበት’ የሚናገሩትን ነገር ማክበር አለባችሁ።
ከዚህ በኋላም መረዳት ያላለባቸው ሰዎችን ለመርዳት ስትፈልጉ ‘ከበሮውን’ አስቀድማችሁ ባትደልቁት ጥሩ ነው። የብዙ ደጋግ ወገኖችን መነሳሳት ለጥቂት ራስ ወዳድ ሰዎች ማስተዋወቂያነት ለማዋል ሲባል በሚደረግ የሚዲያ ላይ ግርግር ከንቱ ሆኖ እንዲቀር አታድርጉት።
ችግር ደርሶባችሁ ወይም ከችግር ለማምለጥ የተሰደዳችሁና በውጭ የምትኖሩ ወገኖች መለስ ብላችሁ አስቡ። ደንዳና አትሁኑ። እናንተ የሸሻችሁትን ችግር አገር ቤት ያሉ ሰዎች የናንተን ፕሮፓጋንዳ ለማሟሟቅ ሲሉ ገብተው ይዳክሩበት ዘንድ መገፋፋት አይገባችሁም። ሰው ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ ማሰብም ተገቢ ነው።
እርግጥ ነው የተሰደደ ሁሉ ችግር ደርሶበት ወይም ችግር አንዣብቦበት ከአገሩ የወጣ አይደለም። ጥቂት የማይባሉ ወገኖቻችን ከአፍርካዊ ድሎትና ምቾት አሜሪካዊ ድህነት ይሻላል ብለው የተጓዙና ለዜግነታቸው ምንም ግድ የሌላቸው ሰዎች መሆናቸውን ልንክድ አይገባም። በሕክምና ሙያ በዶክተርነት ተመርቆ፣ የወቅቱ ገዥ ቡድን ከፍተኛ ደጋፊና የነቃ የፓርቲ አባል በመሆኑ የተቸረውን ወደ አሜሪካ የሚወስድ የትምህርት ዕድል ካገኘ በኋላ አሜሪካ ቀርቶ አንድ ካምፓኒ ውስጥ በተራ ስራተኛነት የተቀጠረውን ጓደኛየን እኔ እንምደማድስታውሰው ሌሎች ኢትዮጵያውያንም የሚያስታውሷቸው ብዙ ወገኖች አሉ።
እናም የኢሳት ችግር የሚፈጠረው እነዚህ ሁለት ቡድኖች (ለምቾት የተሰደዱትና ከመከራ ለማዳን የተሰደዱት) ተቀላቅለው ‘አባረሩን’ እያሉ ሲያማርሩ ነው። ችግር የሚፈጠረው ይህ ቅልቅል በደፈናው ‘አገሬ’ እያለ ሲቆዝም ነው። ኢሳት ላይ በድፍረት ‘ዜግነታችንን ብንቀይር ችግር የለውም፣ የወረቀት ጉዳይ ብቻ ነው’ እያሉ የሚያወሩ ሰዎች ናቸው ተመልሰው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን አሳቢና ተቋርቋሪ መስለው የሚታዩት። እነዚህ ሰዎች ናቸው በአገሩ የሚኖረውን ዜጋ ሊተቹና ሊወቅሱ የሚሞክሩት።
ስለ አለም ዳቻሳ፣ በሳዑዲ ስለተበደሉ ኢትዮጵያውያን፣ ኬንያ ስለገቡ ጋዜጠኞች ወዘተ ብዙ ተወራ እንጅ ብዙ አልተደረገም። ዶላር ወደ ብር መንዝሮ በማውራት ትንሹን ነገር ትልቅ ለማስመሰል ከመሞከር በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ እና ‘ኢትዮጵያዊ’ ስደተኛ በውጭ እያለ የቁንጣ ቁንጦ መዋጫ ብቻ ለምን ይደረጋል ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ነው።
የዓመቱ ትልቅ ሰው ሲመረጥ በድምጽ ሰጭነት የተሳተፈው በ3000 (ሶስት ሽህ) አካባቢ የሚቆጠር ሰው ነው። ከአገር ውስጥ የታሰሩ ሰዎች ብቻ ለምርጫ ቀረቡ ሲባል ከውጭ ደግሞ የኢሳት አክተሮች ብቻ ናቸው ለውድድር የታጩት። አንዳርጋቸው ባይታሰር ኖሮ ‘ትልቅ ሰው ፈኒ’ ፕሮግራም ሆኖ ይቀር ነበረ። ይህ የሚያሳየው የተሳትፎውን ደካማነት ብቻ ሳይሆን የጥምረት ችግር መኖሩን ነው። ዳያስፖራው በጉጅሌ ተቦዳድኖ እያለና ይህን መከፋፈል ወደ አንድነት ማምጣት ሳይቻል የትልቅነት ውድድር በራሱ የመንቀዥቀዥ ፖለቲካ ጨዋታ ነው። ከዚህ ‘የመጎጃጀል’ ክፉ ጠኔ ራሱን ነጻ አውጥቶ ሕብረት ያልፈጠረ ዳያስፖራ ‘ለሐምበርበር ፖለቲካ’ እንጅ ለኢትዮጵያ አይበጅም። እናም በሚሊዮን ሹርቤ ጉዳይ ላይ የታየውን ነገር በዚህ መልኩ ማጠቃለል ይቻላል። ነው። ‘ቀኝህ ስትሰጥ ግራህ አትይ’ የሚለውን ጥበበኛ ቃል በፖለቲካዊ ትርጉሙ ገልብጦ ማየት ተገቢ ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ እሷን የወደዱ መስለው ጥቅማቸውን በሚያሳድዱ ግለሰቦችባ ቡድኖች መወጣጠሯ መቆም አለበት። ‘የሐምበርገር ፖለቲካ’ እና ‘የአምባሻ ፖለቲካ’ ውዝግብ ብዙ ቁም ነገር እየጨፈላለቀ ነው። ይህ ግርግር ለሐምበርገር ወዳጆችና ለአምባሻ አፍቃሪዎች ብቻ የሚጠቅም መንቀዥቀዥ ነው። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም። ይህ መቆም ያለበት ጉዳይ ነው።