//////==== ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ====/////// 

13239377_10206428198804844_3516754715081243243_n

በቅርቡ (ከሁለት ወይም ሦስት) ወራቶች በፊት በንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ መንግስት ያገለገሉትን የሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬን የህይወት ታሪክ ፍንትዉ አድርጐ የሚያሳይ አንድ መጽሐፍ በገበያ ላይ ወጥቷል፡፡
በሁለት መቶ ሰማንያ ስድስት ገፆች የተጠረዘውና በሺበሺ ለማ የተፃፈው ይህ የሕይወት ታሪክ “ቆፍጣና ወታደር ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ” የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡ የመጽሐፉ ሽፋን ቡናማና ነጭ ቀለም የተጐናፀፈው የጄኔራሉ ፎቶግራፍ ሲሆን ከውጭ ሲታይ አንዳች ስሜት ይፈጥራል፡፡ በተለይ ታሪኩን አንብበው ደግመው ፎቶግራፉን ሲመለከቱት፤ የጄኔራሉ አስተያየትና ቅጭም ያለ ፊት የሚነግረን ወሬ፣ የሚያሣየን ሥዕል አለ፡፡ ሕሊናችን ውስጥ አንዳች ነገር ይደውላል፡፡

ጄኔራሉ በ1910 ዓ.ም ወደዚህ ምድር ከመጡ ጀምሮ፣ ያለፉበት የሕይወት ጐዳና ብዙ ነገር ያስተምረናል፡፡ አንድ የሕይወት ታሪክ የአንድን ሰው ታሪክ ዱካ እየተከተለ በተረከ ቁጥር የሚነካቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ አውዶች መልክና ጠረን ማሣየቱ ተገቢ ስለሆነ የእኒህን ጀኔራል ሕይወትም ስንከተል በዘመኑ ማህበረ ፖለቲካዊ አውድ ውስጥ የነበሩ አስተሳሰቦች፣ ንቅናቄዎችና ፍልሚያዎችን ሁሉ እናያለን፡፡

በተለይ ደግሞ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ በኮሪያና በኮንጐ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ የኢትዮጵያና ከዚያም በኮንጐ የአስራ ሰባቱ ሀገራት ሠራዊት አዛዥ በመሆን ስላገለገሉ የወቅቱን አለም አቀፋዊ ፖለቲካ ሣይቀር እንቃኝበታለን፡፡ በኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴና የነፃነት ጥያቄ ውስጥ ሁልጊዜ የሚነሳው የመንግስቱ ንዋይና አበሮቹ ትግል ታሪክም በመጽሐፉ ውስጥ ተካትቷል፡፡

በቀውጢው ቀናት በተለያየ ጐራ ቢቆሙም ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬና ብርጋዲዬር ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ከልጅነታቸው ጀምሮ አብረው ያሳለፉ፣ በአንድ የጦር ትምህርት ቤት የተማሩና ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመንም አብረው የተሰደዱ ባልንጀራሞች ነበሩ፡፡

ጄኔራል ከበደና ጄኔራል መንግስቱ እጅግ የሚቀራረቡ እንደሆነ ለማየት ብርጋዲየር መንግስቱ ንዋይ፤ ሻለቃ ለነበረው ወጣት ጓደኛው የፃፈውን ደብዳቤ ማጤን በቂ ነው፡፡

“ለምወድህና ለፍቅሬ ሻለቃ ከቤ ገብርነት” ይላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ “አዲስ አበባ ስትመጣ ሙዝ ሳትይዝ እንዳትመጣ” የሚል መልዕክትም ይዟል – ደብዳቤው፡፡

የመጽሐፉ ባለታሪክ በኢትዮጵያ የጦር ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ተማሪ ሲሆኑ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ በሲቪል ሹመኝነት የባሌ አውራጃ ገዢ፣ የአሰብ ፌደራሉ መንግስት የወደቡ ሃላፊ፣ የኦጋዴን አውራጃ ገዢ ሆነውም ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም …. ባለቤታቸው ደስታ ገብሩም፤ የከንቲባ ገብሩ ልጅ በመሆናቸውና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ስላላቸው በዚህም በኩል መጽሐፉ የሚያሣየን ሌላ ገጽታ አለ፡፡

በብዙዎች የሚታወቁት ከንቲባ ገብሩ በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በኢየሩሳሌምና አውሮፓ ለአሥር ዓመታት ያህል ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገር ከተመለሱ በኋላ የገጠሟቸውን ፈተናዎች መጽሐፉ በግርድፉ ያሣያል፡፡

የሌተና ጀኔራል ከበደ ገብሬ ታሪክን እያነበብን ስንዘልቅ ለንጉሱ የነበረንን አመለካከት መቀየራችን አይቀርም፡፡ ሰውየው ለሥልጣናቸው ብቻ ሳይሆን ለአገራቸው ለውጥና ዕድገትም ሲታትሩ እንደነበር እንጠረጥራለን፡፡ እኒህ የጦር መኮንን ለዚህ ታላቅ ሹመትና ስኬት የበቁት ከመኳንንት ቤተሰብ የተወለዱ ሆነው አልነበረም፡፡ ከአንድ ደሀ ቤተሰብ ተወልደው፣ አክስታቸው ቤት ተቀምጠው የተማሩ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዓይነት ሕይወት የነበራቸው ሰው ናቸው። ይሁንና ከንጉሰ ነገስቱ ጋር በቅርበት ለመስራትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጦር አዛዥ ሆነው በኮንጐ በማገልገል ታላቅ አድናቆት ከማግኘት ያገዳቸው ነገር አልነበረም፡፡ መኮንኑ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት የትሩማንንም የአድናቆትና የምሥጋና ደብዳቤ ለመቀበል በቅተዋል፡፡ ስለ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ ሳነብ ያስተዋልኩትና ያስደነቀኝ ነገር ጄኔራሉ ነገሮችን ቀድመው የማየት ችሎታቸውና ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ጉዳይ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ መካሪያቸው ባይበዛና የጄኔራሉን ምክር ቢያደምጡ ኖሮ ታሪካቸው በዚያ አይነት ክብር የጐደለው መንገድ አይቋጭም ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ካቀረቡዋቸው ሃሳቦች ባሻገር ወደ አብዮቱ መዳረሻ አካባቢ፣ የኤርትራ ፌዴሬሽን ውል መፍረስ ያመጣቸውን ችግሮች ነቅሰው ከነመፍትሔው ያስቀመጡበት መንገድ፣ የሠራዊቱን ቁጥርና መሠላቸት፣ የኑሮ ውድነትና የሶማሊያ የጦርነት አዝማሚያን በዝርዝር አውጥተው ንጉሱ ሊወስዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ማስቀመጣቸው ጄኔራሉ ትልቅ የመሪነት አቅም እንደ ነበራቸው የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በኤርትራ ለሚኖሩት ሲቪል ወገኖቻችን የነበራቸው መቆርቆር የሰውየውን ቅንነት የሚያሳይ ነው፡፡ ገፅ 273 ላይ የሠፈረው የእጅ ጽሑፋቸው እንዲህ ይላል፡-images
“በነዚህ ዘመናት ውስጥ /አሥር የጦርነት ዓመታት ማለታቸው ነው/ ከወምበዴዎች ጋር በመዋጋት ከጦር ሠራዊትና ከፖሊሶች የሞቱትና የቆሰሉት እንደዚሁም ከታማኙ ኤርትራዊ ብሔራዊ ጦር የተጐዱት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ነው፤ አሁንም እየጨመረ ነው፤ እንደዚሁም በመንግስትን ንብረት ላይ የደረሰው አደጋ ከፍተኛ ከመሆኑም ሌላ በታማኙ ሕዝብ ሕይዎትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት አሁንም አለመቆሙ የጉዳቱን ክብደትና ግምት ከፍተኛ አድርጐታል፡፡” እያሉ ችግሮቹን ካሣዩ በኋላ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የኤርትራ ሕዝብ ከወምበዴው ጋር አብሮ ለመሠለፍ የሚጠብቀው ጊዜ ብቻ ነው ብለው አስጠንቅቀዋል፡፡ ከደብዳቤው መግቢያ ላይም፤ “የኤርትራን ነገር የወታደር ሃይል ብቻውን መፍትሔ ይሆነዋል ብሎ መዳማቱን ከመቀጠል ይልቅ በፅኑ ታስቦበት ሌላ ሁነኛ መፍትሔ እንዲፈለግለት የበኩሌን የቅን ልቦና ምክር በመስጠት…” እያሉ ወደ ቀጣዮቹ ስጋቶች ዘልቀዋል፡፡

እንዲህም ይላሉ…..
“==>በኑሮ መወደድ ምክኛት የተፈጠረዉን ሁኔታ በማብራራት
==>በፓለቲካ ረገድ የግርማዊ ጃንሆይ ን. መንግሥት የገጠመዉን እጅግ አደገኛ ሁኔታ በመግለጽ…
==>በኢኮኖሚ በኩል አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ በእኔ ግምት እጅግ መጥፎ መሆኑን በማስረዳት….
==>የኤርትራን ነገር የወታደር ሃይል ብቻውን መፍትሔ ይሆነዋል ብሎ መዳማቱን ከመቀጠል ይልቅ በፅኑ ታስቦበት ሌላ ሁነኛ መፍትሔ እንዲፈለግለት የበኩሌን የቅን ልቦና ምክር በመስጠት…” ወ.ዘ.ተ. እያሉ በርካታ ነገሮችን ያለምንም ፍርቻ ለንጉሡ ይጽፉ ነበር…..

እናም ይህ የፌሰ-ቡክ ቡድን (ግሩፕ) …. እኝህ ኩሩ ጄኔራል እንደ አገራችን ዘመን አቆጣጠር የካቲት 18 ቀን 1956 ዓ.ም. “ጥብቅ ሚሰጥር” በማለት በራሳቸዉ የእጅ ፁሁፍ የኤርትራን ችግርን ጨምሮ ሌሎችንም አገሪቷ ያጋጠማትንና ሊያጋጥማት ይችላሉ ያሉትን በርካታ ጉዳዬች መፍትሄ ይሆናሉ ካሏቸዉ ነገሮች ጋር ለአፄ ሀይለሥላሴ የፃፉላቸዉን ደበዳቤ ታነቡት ዘንድ …. አንብባችሁም ታስቀምጡት ዘንድ ወደ እናንተ አቀርብን።

https://drive.google.com/…/0B1Z2sddQH9yRRzBwbGlCQ3pre…/view…

Shagiz Shagi's photo.