ወያኔ ለተራቡ ወገኖች እርዳታ ማድረግ የምትችሉት እኔ ስፈቅድና በእኔ በኩል ብቻ ነው አለ

የወያኔ ተላላኪዎች በኩዌትና ባህሬን ነዋሪ ለሆኑ ኢትዮጵያውያኖች ባስተላለፉት መግልጫ አዘል ትእዛዝ እንዳሉት ከሆነ “በረሃብ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረጉ እርዳታዎችና ገንዘብ ማሰባሰቦች እኛ ስንፈቅድና በእኛ አማካኝነት ብቻ ነው” ብለዋል።

የመግለጫው ሶስተኛ አንቀጽ እንዲህ ይነበባል፣

“…በሌላ በኩል ጉዳዩ ከልብ አሳስቧችሁ ነገር ግን ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለው ሁኔታ እንዲሁም ሕጋዊ አካሄድን ሳይከተል “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል የተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎችን በመጠቀም ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ የምትገኙ ሁሉ ይህንን ህገወጥ ተግባር እንድታቆሙ፣ ሌሎቻችሁም በየዋህነት በእንቅስቃሴው እንዳትሳተፉ እንጠይቃለን”።

“ችግሩ እስካሁን ድረስ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ አልወጣም፣ በሰዎች ላይም አደጋ አልደረሰም” ሲል ያተተው መግልጫ… በመጨረሻም መንግስት እርዳታ የሚፈልግ ከሆነ እኛ ስንጠይቃችሁ ያን ጊዜ ገንዘቡን ለኛ ትሰጣላችሁ ብሏል።

ይህ በዚህ እንዳለ ታዋቂው የመብት ተሟጋች አርቲስት ታማኝ በየነ እና ሌሎችም የሚሳተፉበት “ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት” በመባል የሚታወቀው የሰብአዊ መብት ማኅበር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫማህበሩ ከዚህ ቀደም በሳውዲ አረብያ ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ፈጥኖ እንደደረሰ ሁሉ አሁንም አግባብ ካላቸው የአለም ዓቀፍ ረድኤት ድርጅቶች ጋር በመነጋገርና በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በፍጥነት በርሃብ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ ለማሰባሰብ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በስልጣን ላይ ያለው የወያኔ አስተዳደር ጥንት ጫካ በነበረበት ሰዓት በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከረሃብተኛው አፍ ነጥቆ መውሰዱን ቢቢሲ እና በወቅቱ የወያኔ አመራር አባል የነበሩት አቶ ገብረመድህን አርአያ ማጋለጣቸው ይታወሳል።