ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ መለስ ዜናዊ ባንዳ ነው ይሉታል፣ ህወሓትን ደግሞ ከሃዲ!

‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ የውጭ ወራሪ ኃይል በወጋት ቁጥር ከጠሏቶቿ ጎን ተሰልፈው የሚወጓት ልጆች አታጣም፡፡ ጣሊያንም ሆነ እንግሊዝ ሊወጉን በመጡ ጊዜ ሁሉ በባንድነት ከጎናቸው ተሰልፈው አገራቸውን የወጉ የወገንና የአገር ጠላቶች በመኖራቸው ብቻ አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የሶማሊያ መንግስት ለወረራ ሲዘጋጅ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነፍጥ አንስተው የሚወጓትና ስልጣን ለመጨበጥ ጉጉት የነበራቸው ድርጅቶችን የወረራው አካል አደረጋቸው፡፡

‹‹ሰይድ ባሬ ወረራውን በሚያካሂድበት ጊዜ የተጠናከረ ጦር እንዳይገጥመው ኢትዮጵያን ለማፍረስ አላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ከሃዲ ድርጅቶች በተቀነባበረ ስልት በምስራቅ፣ በደቡብና በሰሜን ኢትዮጵያን እንዲያጠቁና የኢትዮጵያን ከፊል ጦር በውጊያው ጠምደው እንዲይዙ ፈለገ፡፡ ይህንን ፍላጎቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻለው ኤርትራን ለመገንጠል የሚዋጋውን የሻዕቢያ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂን፣ ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥሎ ነፃ የትግሬ መንግስት ለመመስረት ኢትዮጵያን ሲወጋ የነበረውን የህወሓት መሪ መለስ ዜናዊን፣ ኦሮሞን ነፃ እንዲያወጣ ሶማሊያ የፈጠረችውን ነፃ አውጭ ድርጅት የሚመራውን ዋቆ ጉቱን፣ የሲዳማ ነፃ አውጭ ድርጅት ተብሎ በሶማሊያ የተመሰረተውን ድርጅት የሚመራውን ወልደአማኑኤል ዱባለን ሞቃዲሾ ሰብስቦ መመሪያ ሰጣቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በተለያዩ አገሮች የሚዘዋወሩት በሶማሊያ ፓስፖርት እንደነበር እዚህ ላይ ሊሰመርበት ይገባል፡፡››

( እኛና አብዮቱ ገፅ 363)