በአሁኑ ወቅት በአይ ኤስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ተገለጸ

በአሁኑ ወቅት በአይ ኤስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2007(ኤፍ.ቢ.ሲ) በግብጽ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር ለፋና ብርድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ አንዳንድ አካላት አሁንም በርከት ያሉ ኢትዮጵያዊያን በአይ ኤስ ቁጥጥር ስር ናቸው በማለት የሚያሰራጩት ወሬ ትክክል አለመሆኑን እና ኤምባሲው ባደረገው የማጣራት ስራ በሊቢያ በአይ ኤስ እጅ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሉም ብለዋል።

በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በህገ ወጥ ደላሎች ማቆያ ውስጥ እንጂ አይ ኤስ እጅ እንዳልወደቁም አምባሳደር ሙሃሙድ ድሪር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አጉረው የያዙት ደላሎችም የሶማሊያ፣ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ሲሆኑ፥ እነዚህ ደላሎችም ወደ ጣሊያን እናሸጋግራቹዋለን በሚል ነው ሰደተኞችን አጉረው ያሰቀመጡት ብለዋል።

አሁን በሊቢያ ባለው ችግር ምክንያት ህገ ወጥ ደላሎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል አስቸጋሪ ቢሆንም፥ ወደ ፊት ግን ደላሎቹን ለህግ የማቅረብ ስራ ይሰራልም ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሊቢያ ለማውጣት ከአልጄሪያ፣ ሱዳን እና ሌሎች አጋር ሀገሮች ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም በራሳቸው ፍቃድ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተመዘገቡ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

አንዳንድ ወገኖች እና የውጭ ሚዲያዎች በርከት ያሉ በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው አይ ኤስ እጅ ናቸው እያሉ የሚያሰራጩት ዘገባ መሰረተ ቢስ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም አንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች እና ግለሰቦች ህዝቡ በድርጊቱ ማዘኑን እና መቆጣቱን በመጠቀም ሁኔታውን ለርካሽ የፖለቲካ መጠቀሚያነት እያዋሉት ነው ሲሉ አምሳባደሩ ወቅሰዋል።

በመሆኑም እነዚህን በንጹሃን ኢትዮጵያዊያን ደም ርካሽ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን ህብረተሰቡ በጋራ በመሆን ሊከላከላቸው እና ሊያወግዛቸው እንደሚገባ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር አሳስበዋል።
በታደሰ ብዙዓለም