ያው በዛሬው የኢብካኮ የክርክር መድረክ ላይ እድል ባናገኝም የሰማያዊ ፓርቲን የፌደራሊዝም እይታ እና ፖሊሲ፤ አሁን ባለው የፌደራሊዝም አወቃቀር ላይ ያለንንም ትችት ላካፍላችሁ – የአንድነት፣ የከለላና የዋስትና ምልክት በሆነው በጃንጥላችን ተሰባስባችሁ ተወያዩበት
March 20, 2015 Derege Negash – ደረጀ ነጋሽ

ከሰማያዊ ፓርቲ

የሀገር አስተዳደር አወቃቀር

በኢትዮጵያ ጎሳንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራላዊ ስርአት ከተዋቀረበት ጊዜ ጀምሮ በአብዛኞቹ የአገሪቷ ክልሎች ተደጋጋሚ የሆነ የጎሳ ግጭቶች መከሰታቸውን ኢሰመጉ እና ተመሳሳይ ድርጅቶች በየጊዜው ባወጣቸው መግለጫዎች ገልጸዋል፡፡ በአማራና በኦሮሞ፣ በኦሮሞና በሱማሌ፣ በወላይታና በጋሞ፣ በወላይታና በሲዳሞ፣ በአኙዋክና በኑዌር ፣በአኝዋክና በሱርማ ፣በሱርማና በዲዚ ተወላጆች መካከል የተከሰቱት ግጭቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የሕወሀት/ኢህአዲግ መንግስት የሚከተለው የጎሳ የፌዴራል ስርዓት የእርስ በእርስ ግጭቶችን እንዲባባሱ እና በጎሳዎች መካከል አስከፊ ቅራኔ እንዲኖር አድርጓል፡፡ የጎሳ የፌደራል ስርዓት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የጎሳ ግጭቶች የተካሔዱ ሲሆን ለእነዚህ ግጭቶች ዋና መንስኤው የጎሳ የፌደራል ስርዓቱ ነው፡፡ በአርባ ጉጉ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በመተከልና በቤንች ማጂ፣ በጎጂ ኦሮሞና በጌዲኦ ህዝብ መካከል፣ በወላይታና በጋሞ፣ በአኙዋክና በኑዌር፣ በአማራ እና በአፋር፣ በአፋርና በሶማሌ፣ በአፋርና በኦሮሞ፣ በኦሮሞ እና በሶማሌ መካከል በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች የጎሳ ፌደራል ስርዓቱ ውጤት ናቸው፡፡ ለአስረጅነት ያህል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ በተለያዩ ጊዜያት ያጠናቀራቸውን የጐሳ ግጭቶች እንደሚከተለው በምሳሌነት ቀርበዋል፡፡

መስከረም 1999 በኦሮሚያ ክልል፣ በአባይ ገላን ወረዳ እና በአማሮ ኬሎ ወረዳ በደቡብ ክልል በከዶራ እና በጐጀ ኦሮሞዎች መካከል የተካሔደው ግጭት 11 ሰዎች ሲሞቱ 18 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ከ662 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል በርካታ ንብረቶች ተዘርፈዋል፡፡
ታህሳስ 2000 በሲዳማ እና በጐጂ ኦሮሞዎች ተወላጆች መካከል የተካሔደ ግጭት አራት ሰዎች ሲሞቱ 5 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ከ800 በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ በርካታ ንብረቶች ወድመዋል፡፡
መጋቢት 2000 በደቡብ ክልል በሚገኘው በቡርጅ ወረዳ እና በኦሮምያ ክልል በሚገኘው ጉርጅ ዞን በቡሌ ሆራ ወረዳ መካከል የተፈጠረው ግጭት 23 ሰዎች ሲሞቱ 8 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል 5 ሚሊዬን የሚገመት ንብረት ወድሟል በርካታ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
ግንቦታ 2000 በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በጉምዝ እና በምስራቅ ወለጋ በሚገኙ በኦሮሞ ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጡ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ሐምሌ 1994 በዲዚ እና በሱርማ ተወላጆች አባላት መካከል በተፈጠረ ግጭት 31 ሰዎች ሲሞቱ 5 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 1300 ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ 152 ቤቶች ተቃጥለዋል 166 ከብቶች ተዘርፈዋል
ህዳር 1996 በምዕራብ ሐረርጌ በሜይስ ወረዳ በኦሮሞ እና በሱማሊያ ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት 19 ሰዎች ሲሞቱ 21 ሰዎች ቆስለዋል፣ 34 ግመሎች ተዘርፈዋል፣ 27 ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡
1994 በጋምቤላ በኑዌር እና በአኝዋክ ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከመቶ በላይ ሰዎች ሲሞቱ 42 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል በርካታ ሰዎች ወንዝ ገብተው ሞተዋል
ጥር 1997 በሐረርጌ ዞን በኦሮሞና በሱማሌ ተወላጆች መካከል 18 ሰዎች ሲሞቱ 31 ሰዎች ቆስለዋል
ነሐሴ 1998 በምስራቅ ወለጋ በጊዳ ኪርሙ ከተማ በኦሮሞና በአማርኛ ተናጋሪ ዜጐች መካከል በተከሰተ ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ አራት ሰዎች ቆስለዋል
ነሐሴ 1992 በቦረና ዞን በኦሬሮ ወረዳ በጉጅ እና በገሪ ተወላጆች መካከል 75 ሰዎች ሲሞቱ 33 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
የካቲት 1992 በሰሜን ሸዋ በኦሮሞ እና በአማራ ተወላጆች መካከል ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች የህይወት እና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
መስከረም 1993 በምስራቅ ወለጋ በኦሮሞና በአማራ ተወላጆች መካከል ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች የህይወት እና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
ታህሳስ 1992 በሰሜን ኦሞ በወላይታ እና በጋሞ ተወላጆች መካከል ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች የህይወት እና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
ህዳር 1991 በጉጅ እና በጌዲዬን ተወላጆች መካከል ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች የህይወት እና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

በኢትዮጵያ ሰላም እና ዕድገት ለማምጣት የጐሳ ፖለቲካ ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አርቃቂዎች አበክረው ቢገልፁም የጐሳ ፖለቲካ ግጭት እንደሚጋብዝ እና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ሰፊ ትንታኔዎች በየጊዜው ሲቀረቡ ቆጥተዋል፡፡ ለምሳሌ እያንዳንዱ ግለሰብ /ዜጋ የእሱን/ የእሷን ቋንቋ ከሚናገሩ የጐሳ አባላት ርቆ ሊገኝ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለረዥም ጊዜ አብረው በመኖራቸው ምክንያት እና በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ተሰባጥረው ነው የሚገኙት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ80 ብሔረሰቦች በላይ በያዘች ሀገር ውስጥ የጐሳ ፖለቲካ ሊተገበር አይችልም፡፡ እያንዳንዱ ጐሳ የራሱ የሆነ ክልላዊ መንግስትን የመመስረት ፍላጐት ስለሚኖረው በዘጠኝ ክልሎች የተከፋፈለው ክልላዊ መንግስት በቀጣይ ወደ ተለያዩ ክልላዊ መንግስታቶች የመሰነጣጠቅ አደጋ ይጋለጣሉ፡፡

የሕወሀት/ኢህአዲግ የፌዴራል ስርዓት ህዝቡን ከፋፍሎ ለመግዛት የተጠቀመበት የፖለቲካ ቀመር እንጂ ምንም ዓይነት የፌዴራል ስርዓት ሽታ የለውም፡፡ ለምሳሌ ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት የጐሳ ፖለቲካ ንድፈ ሀሳቦች በአራቱ የአጋር የኢህአዲግ ድርጅቶች ላይ የማይተገበሩ የፖለቲካ ስሌቶች ናቸው፡፡ እንደ አስረጅነት ለመጥቀስ ክልላዊ መንግስቶች ለፌዴራል መንግስት ታዛዥ ናቸው እንጂ ምንም ዐይነት የፖለቲካ ኃይልና ስልጣን የላቸውም፡፡ ስለዚህ የኢህአዲግ ስርዓት አቀንቃኞች የጐሳ ፖለቲካ የጐሳ ልዩነትን ከማቻቻል ይልቅ የጐሳ ልዩነትን ወደ ግጭት የሚጋብዝ እንደሆነ ቢረዱትም ህዝቡን/ ዜጐችን ለመከፋፈል ስለጠቀማቸው የጐሳ ፖለቲካ ቅኝትን አንግበው ተነስተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ግጭቶች ሳይቀሩ ዋና መሰረታቸው መንግስት የሚያራምደው የጎሳ ፖለቲካ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ስርዓት /የጎሳ ፖለቲካ/ ግጭት እንደሚጋብዝ በተለያዩ ምሁራን የተገለፀ ሲሆን በእኛ ሀገር የተከሰቱት ግጭቶችም የጎሳ ፖለቲካ ውጤት እንደሆኑ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ (አሰፋ ፍሰሃ 2006፣ ደረጀ ፈይሳ 2006፣ ሳሪህ ቫጋን 2006) ፡፡
ስለዚህ ለፍጥጫና ለግጭት መነሻ የሆነው የጎሳ የፌዴራል ስርዓት የሀገሪቱን ህዝብ ልዩ ልዩ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶችና አመለካከቶች ባካተተው የፌደራል ስርዓት ይቀየራል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ይህን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት የሀገር አስተዳደር በፌደራላዊ ስርዓት በተዋቀሩ ክፍለ ሀገራት የተከፋፈለ ይሆናል ብሎ ያምናል፡፡ የፌዴራል መንግስት አወቃወር መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን፣ የህዝብ አሰፋፈርን፣ ለልማትና አስተዳደር አመችነትን፣ ቋንቋና ባህልን፣ ታሪክን ፣ የህዝብ ፍላጎትና ሌሎች ማህበራዊ ትስስሮችን መሰረት ያደረገ ሲሆን በየደረጃው ህዝቡ ራሱን የማስተዳደር መብቱን የሚረጋግጥባቸው ምክር ቤቶች ይኖራሉ፡ የፌዴራል ስርዓቱ አከላለል ሂደት እንደ ሕወሀት/ኢህአዲግ ቋንቋን ብቻ ያማከለ መሆን የለበትም፡፡ ቋንቋን ያማከለ የፌዴራል የአከላለል ስርዓት የማያግባቡ ሁኔታዎችን እንደፈጠረ ከሕወሀት/ኢህአዲግ ስርዓት መማር ተችሏል፡፡

በዚህ መሰረት የፌደራል ክልሎች የህዝብን ፈቃደኝነት ታሪካዊና ባህላዊ ትስስርን፣ የህዝብን አሰፋፍና የመልክዓ ምድርን አቀማመጥ፣ የልማት አመችነትን፣ የአስተዳደር ቅልጥፍናን የመሳሰሉትን መመዘኛዎች ባገናዘበ መንገድ የፌዴራል ስርዓቱ ይዋቀራል፡፡ በዚህ የሀገር አስተዳደር አወቃቀር በፌደራሉና በክልል መንግስታት መካከል ያለው የስልጣን ግንኙነት ሚዛናዊና ግልፅ በሆነ የህግ ስርዓት እንዲመራና በሀገራችን የሚቋቋመው የፌደራል ስርዓት ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል አወቃቀር ይኖረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሰላም አንድነት ተስፋ
ሰማያዊ ፓርቲ

Like · ·